በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በደቡብ ኦሞ ዞን ቱርሚ ከተማ ተወያዩ ፡፡
የውይይት መድረኩን ጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና የደቡብ ክልል መንግስት በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይለማርያም ተስፋዬ ÷ ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ የነበረው ስርዓት የህዝቦችን የበላይነት እና የዴሞክራሲ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የቡድኖችንና የግለሰቦችን ፍላጎት ማሟላት ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስልጣን ካጣበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ብጥብጥ እና ትርምስ በመፍጠር አለመረጋጋት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ አላማውን ለማሳካት ለሚጥሩ አካላት በጀት መድቦ ህዝቦችን ለከፋ ስቃይ መዳረጉን አስረድተዋል።
የውስጥ እና የውጭ ሀይሎች ተላላኪ መንግስት እንዲፈጠር ለማድረግ የጀመሩት ጥረትም በጋራ ትግል ይከሽፋል ሲሉም አስረድተዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙሁራን በዘርፉ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የድርሻቸውን ሚና እንዲወጡ መጠየቃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡