የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎበኙ።
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ክንውን ተመልክተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላም ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ በስፍራው ፀሎት አድርሰዋል።
የኢትዮጵያ የኀይማኖት ተቋማት ጉባዔ በወርኃ ጳግሜን ለ5 ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ ፀሎት እንዲካሄድ ማወጁ ይታወሳል።
የጉባዔው ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ የአንድነትና ሉዓላዊነት ተምሳሌት በሆነው ግድብ በአዲስ አመት ዋዜማ በመገኘታችን ተደስተናል ብለዋል።
የ2014 ዓ.ም አዲስ አመት ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋና ሰላም ይዞ እንዲመጣም እንመኛለን ነው ያሉት።
የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት ግድቡን የደህንነት ስጋት ነው በማለት ባልተገባ መልኩ ጫና ለማድረስ ቢሞክሩም ግንባታው በስኬት እየተከናወነ ሙሌቱን በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሰረት እየተከናወነ በመሆኑ ሁላችንንም አስደስቷል ብለዋል።
የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት መጠቀም ከተቻለ ለሁሉም የሚበቃ መሆኑን ጠቅሰው “እኔ ብቻ ልጠቀም” የሚለው እሳቤ ግን በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም ነው ያሉት።
በመሆኑም ግብፅና ሱዳን “እኔ ብቻ ልጠቀም” የሚለውን እሳቤን በማስወገድ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ራሳቸውን ማዘጋቸት ይገባቸዋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ህዳሴ ግድብ የሁላችንም የጋራ ሃብትና የልፋት ውጤት በመሆኑ በቀጣይም የህዝቡ ድጋፍና ትብብር እንዲቀጥል የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች ጥሪ አቅርበዋል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በስፍራው በመገኘት ለሃይማኖት አባቶቹ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
በጉብኝታቸው የእያንዳንዱ ቤተ እምነት አባቶች መልክት ያስተላለፉ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን የአንድነት፣ የልማት፣ የብልፅንና ተምሳሌት የሆነው ታላቅ ፕሮጀክት በዚሁ ደረጃ በመድረሱ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!