ህብረተሰቡ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ ጥቆማ መስጠት አለበት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ ጥቆማ መስጠት እንዳለበት የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
እየተስተዋለ የለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመከላከል ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል፡፡
በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው ዋጋ ማረጋጊያ ግብረ-ሀይል ሰሞኑን በኦሮሚያ ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ አማራ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በንግዱ ዘርፍ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ የመስክ ቅኝት አድርጓል፡፡
ግብረ-ሀይሉ በመስክ ምልከታው ወቅት በንግዱ ዘርፍ ያገኛቸውን ችግሮችና አሁናዊ ሁኔታዎች ሪፖርት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አቅርቧል፡፡
በዚህም ምርት መደበቅ፣ ሱቅ መዝጋት፣ የሽያጭ ደረሰኝ ያለመስጠትና ቢሰጡም የሚሸጡበት ዋጋና ደረሰኝ ላይ የሚጻፈው ዋጋ መለያየት፣ የዋጋ ዝርዝር ያለመለጠፍ ች፣ የደላሎች በሁሉም የግብይት ቦታዎች ደላላዎች መግባት የተስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸው ተመላክቷል ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መንግስት የህልውና ዘመቻ እያካሄደ ባለበት ወቅት የኢኮኖሚ አሻጥር መፍጠር በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ እኩይ ተግባራት ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡
ለኑሮ ውድነቱ መባባስ እንደ ትልቅ ተግዳሮቶች ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ወስጥ በግብይት ሂደቱ የህገ-ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት እንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ እነዚህ እና መሰል የስርዓት አልበኝነት ችግሮችን ከስሩ ለማድረቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራ ግቡን ሊመታ የሚችለው የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ ህገወጥ ደላሎችንና ማንኛውንም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ሲመለከት ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ቀና ትብብር እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!