ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ስራ ዝግ እንደሚሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው እና ህዝበ ውሳኔ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በነገው ዕለት ስራ ዝግ ሆኖ እንደሚውል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሐረሪ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚከናወነውን ድምጽ አሰጣጥ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ ባልተሰጠባቸው ቀሪ ምርጫ ክልሎች እና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ይከናወናል።
በዚህም መሰረት ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሐረሪ ክልል፣ በሶማሌ ክልል፣ በደ/ብ/ብ/ህ ክልል በምእራብ ኦሞ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ በቤንች ሸኮ ዞን፣ በሸካ ዞን፣ በጌዲዮ ዞን፣ በሃድያ ዞን፣ በጉራጌ ዞን፣ በጋሞ ዞን፣ በካፋ ዞን፣ በወላይታ ዞን ፣ በዳውሮ ዞን፣ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ እና በኮንታ ልዩ ወረዳ መሆናቸውን ነው ቦርዱ ያስተወቀው።
በዚህም መሰረት ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች እና ዞኖች የሚገኙ የፌዴራል እና የክልል መንግስታዊ ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል ተቋማት በዕለቱ የስራ ተቋመቸውን ዝግ እንዲያደርጉ ቦርዱ ማሳሰቢያ ስጥቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የእለት ተእለት አገልግሎት ሰጪዎች ፥ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት ወዘተ በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ ማከናወን የሚችሉ ሲሆን የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።
የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም በተጠቀሱት ክልሎች እና ዞኖች ዜጎች ድምጽ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችን እና እቅዶችን እንዳይዙ እና እንቅስቃሴያቸውን ድምጽ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ እንደሚያበረታ ነው የገለጸው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!