Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ደባ እየፈጸመ ነው – ኦነግ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ደባ እየፈጸመ መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ገለጸ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለውስጥ በስውር እጃቸው የኢትዮጵያ ሕዝብን ሲያውኩ የቆዩት አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ሕብረታቸውን ይፋ ካደረጉ ሰንብተዋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት የመንግሥት ሥልጣን በተቆጣጠረበት ዘመን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በአሸባሪነት ማስፈረጁ ይታወሳል፡፡

አሁን የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ሲል “ሸኔ” ከተባለ አሸባሪ ቡድን ጋር በሕብረት እንደሚሰራ በይፋ ገልጿል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉት÷ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በመንግሥት የቀረበለትን የሰላማዊ ትግል ጥሪ ተቀብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ኦነግ ለረጅም ዓመታት ካደረገው የትጥቅ ትግል ይልቅ የኦሮሞ ወጣቶች ባካሄዱት ሰላማዊ ትግል ያመጡትን ለውጥ ማንሳት ይቻላል በማለትም የሰላማዊ ትግል አስፈላጊነትን ያነሳሉ፡፡

እንደ አቶ ቀጄላ ገለጻ÷ ከሰላማዊ ትግል ውጭ ለኢትዮጵያ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፋይዳ የለውም፡፡

በዚህ ወቅት በትጥቅ የታገዘ ትግል ማድረግ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲደፈር በር መክፈት መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡

“ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ያበረው አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪካዊ ደባ እየፈጸመ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል” ነዉ ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ፡፡

አሸባሪው ሕወሓት የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ሁሉ በደል መረሳቱ የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተው÷ አሸባሪው ሸኔ ደግሞ ዛሬ በእንዲህ ዓይነት መልኩ መምጣቱ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥምረቱም አሸባሪው ሕወሓት እንደለመደው የኦሮሞን ሕዝብ በመከፋፈል የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት አሸባሪው ሸኔ በሚያደርገው የሽብር እንቅስቃሴ የኦሮሞ ሕዝብ እየተሰቃየ መሆኑንም ነዉ አቶ ቀጄላ ያነሱት፡፡

ሕዝቡ ፊት ለፊት ወጥቶ አሸባሪውን ሸኔ እንዲቃወምና እንዲታገልም ምክትል ሊቀመንበሩ ጥሪ ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.