ድጋፍ ስለተደረገልን እስካሁን የከፋ ችግር አላጋጠመንም – በደሴ ከተማ የተጠለሉ ወገኖች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባባር እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ እስካሁን ድረስ የከፋ ችግር እንዳልገጠማቸው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች ተናገሩ።
የአዋሽ ኮምቦልቻ ሐራ ገበያ ባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ሠራተኞች በደሴ እና ኮምቦልቻ ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች 2 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጭ የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ከአካባቢያቸው በድንገት ሲወጡ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደነበሩ እና አሁን መንግስት መጠለያ በማዘጋጀት የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ በማቅረብ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ስጋታቸው እንደቀለለ ተናግረዋል፡፡
ከቄያቸው ከተፈናቀሉ ከአንድ ወር በላይ ቢሆናቸውም ÷ መንግስት ህብረተሰቡን እና ተቋማትን በማስተባበር ባደረገላቸው ድጋፍ እስካሁን ለከፋ ችግር እንዳልተጋለጡ ገልጸዋል።
በድጋፉ ልጆቻችን አልተራቡም፣ የሚለብስቱም አላጡም፣ የከፋ ችግርም አልገጠመንም ብለዋል፡፡
በተለይ የደሴ ከተማ ህዝብ ከሚበላው ቀንሶ ልጆቻችንን ለማስደስት እያደረገ ያለው ሁለተናዊ ድጋፍ የወሎን የአብሮነትና የመረዳዳት ባህል በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
የደሴ ከተማ ህዝብ ከሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ባሻገር መንግስት ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ ባደረገላቸው የመጠለያ፣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል በበኩላቸው÷ ለተፈናቃዮች የሚመጣውን ድጋፍ በፍትሃዊነት ለሁሉም ለማዳረስ የተፈናቃይ ተወካዮችን በማካተት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዋሽ ኮምቦልቻ ሐራ ገበያ ባቡር መስመር ዝርጋት ፕሮጀክት ሠራተኞችም 2 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጭ የምግብ ዱቄት፣ የአልባሳትና የውሃ መያዣ ታንከሮችን ለተፈናቃዮቹ ለግሰዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ ድጋፉን ሲያስረከቡ እንዳሉት÷ ተፈናቃዮችን መንከባከብና ማገዝ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
የፕሮጀክቱን ሠራተኞች በማስተባበር ድጋፍ ማምጣታቸውን ጠቁመው÷ ለባቡር ግንባታው የእርሻ ማሳቸውን የሰጡ አርሶ አደሮችም ጭምር በመፈናቀላቸው ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶኛል ብለዋል።
በቀጣይ እስኪቋቋሙ ድረስ በገንዘብ፣ በግንባታ ቁሳቁስና በሙያም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን