‹‹በእርዳታ ሽፋን ህገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በተገኙ አካላት ላይ የተወሰደው እርምጃ የሚያስመሰግን ነው›› – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
አዲስ አበባ፣ መሰከረም 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) መንግስት በእርዳታ ሽፋን የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል ህገ ወጥ ተግባር ተሰማርተው ባገኛቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ተገቢ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታወቁ።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንደገለጹት÷ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በአንድ ሀገር ሰብዓዊና ቁሳዊ ችግሮች ሲፈጠሩ እገዛ ለማድረግ መግባታቸው የተለመደ ነው ፤ይህንን ተግባር ሲያከናውኑ ግን የሀገሪቱን ህግ የማክበር ግዴታ አለባቸው።
እንቅስቃሴያቸው ሀገር አፍራሽ መሆኑ እየታወቀ እርምጃ አለመውሰድ ሀገርን የሚጎዳ ፤ክብርንም የሚነካ ነው ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ መንግስት የህዝቦቹን ደህንነትና የሀገሩን ክብር ለማስጠበቅ ካለበት ሃላፊነት አንጻር የወሰደው እርምጃ የሚያስመሰግን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው ግለሰቦች ባላቸው ተሰሚነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የጠቀሱት ፕሮፌሰር በየነ፣ ምንም ያድርጉ ምን ከሀገር ክብርና ከህዝብ ጥቅም የሚበልጥ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
የትኛውም የውጭ ሃይል በእርዳታና በሌላ ጉዳይ አመካኝቶ የፈለገውን እንዲያደርግ የሚፈቅድ ህግ የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእርዳታ ሽፋን ሰላሟን የሚያደፍርሱና ሉዓላዊነቷን የሚዳፈሩ ተግባራት ሲፈጸም እያየች ዝም አትልም፤የተወሰደው እርምጃም በማስረጃ ላይ ተመስርቶ እስከ ሆነ ድረስ ተገቢ ነው ብለዋል።
እርምጃው የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው መልዕክት ያስተላለፈ እንደሆነም ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
እርዳታን መያዣ አድርገው በአንድ ሀገር ጉዳይ እጃችንን ካላስገባን ለሚሉ ቦታ መስጠት አያስፈልግም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ በእርዳታ ስም የሚመጣውን ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የማምረት አቅሙን አሳድጎ ህዝብን ከተረጂነት ማውጣት እንደሚገባው፤ ህዝቡም ጠንክሮ በመስራት ጫናውን መቀልበስ እንዳለበት አሳስበዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!