በፖለቲካ ልዩነት ለዘመናት የዘለቀውን መጠፋፋት ለማስቀረት መሠረት የጣለ እርምጃ
አዲስ አበባ፣ መሰከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የካቢኔ ሹመት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች መካተታቸው በፖለቲካ ልዩነት ለዘመናት የዘለቀውን መጠፋፋት ለማስቀረት መሠረት የጣለ እርምጃ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
አዲስ የተመሰረተው መንግስት የሀገርና የህዝብ ጥቅም ያስቀደመ መሆኑ ተመልክቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ የምዕራብ ጎንደር ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ አዲስ የተመሰረተው መንግስት የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየ ነው።
ከዚህ በፊት ከገዢው ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች የሚገደሉበት፣ የሚሳደዱበት በግፍ ታስረው የሚሰቃዩበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በፌደራል መንግስት በሚኒስትርነት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርና በክልሎች በቢሮ ሃላፊነት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን መሾም መቻሉ ለአገራችን የመቻቻል ፖለቲካ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በሀገር ጉዳይ ላይ ይበጃል የሚሉትን ሃሳብ በነጻነትና በግልጸኝነት ከማራመድ ባሻገር በቅንነትና ታማኝነት ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት እድል መፈጠሩ መልካም ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ፓርቲ የመተማ ወረዳ ሊቀመንበር አቶ ተሾመ ሞላ በበኩላቸው÷ በየደረጃው በተሰጠው ሹመት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካተታቸው በሀሳብ ልዩነት ውስጥ አብሮ ለመስራት አዲስ ልምምድ የፈጠረ ነው ብለዋል።
እስካሁን የነበረውን የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግባራት ከመተቼት፣ ከመጠየቅና ከማጣጣል በመውጣት የጋራ አገራዊ ሃላፊነት ለመውሰድ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
“ሁሉም ፖለቲከኛ ለሀገርና ህዝብ በጋራ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ያሉት ሰብሳቢው ÷ ሁሉም አካላት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ወደ ውጤት በመቀየር የጋራ ቤታችንን ሰላሟን ለመጠበቅና ለመገንባት መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!