የዘንድሮው የገና በዓል የሚከበረው ሀገራችን በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ወደ ትንሳኤዋ እያመራች ባለችበት ወቅት ነው-አቶ እርስቱ ይርዳ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28 ፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ የእየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የ2014 ዓ.ም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት÷ የዘንድሮውን የገና በዓል የተለየ የሚያደርገው ሀገራችን ኢትዮጵያ በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ወደ ትንሳኤዋ እያመራች ባለችበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል።
አክለለውም ሙሉ ትኩረታችን በድህረ ጦርነት የሚያጋጥሙንን ችግሮች ተጋፍጠን የኢትዮጵያን ትንሳዔ ከፍ ማድረግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጥንትም የሚገጥሟትን ፈተናዎች በአሸናፊነት ስትወጣ መቆየቷን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ሀገራችን የማይነጥፉ ጀግኖች እስከ አሏት ድረስ የማንቋቋመው ችግር የለም ነው ያሉት።
ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ሀገር በቀላሉ ማፍረስ እንደማይቻል ዘንድሮ ከገጠመን ጦርነት መረዳት ይቻላል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሀት እና አሸንጉሊት መንግስት እንዲመሰረት ፍላጎች ያላቸው አንዳንድ የውጭ ሀይሎች በቀቢጸ ተስፋ ተነሳስተው በሀገራችን ያወጁት ጦርነት በጀግኖች ልጆቻችን ተጋድሎ ለድል በቅተናል ሲሉ አክለዋል።
ተገደን የገባንበት ጦርነት ከአሸባሪው ህወሀት ጋር ብቻ ሳይሆን እሱን በፋይናንስና በሎጂስቲክ ከሚደግፉ አካላትም ጭምር መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በሀገር ጉዳይ አንድ ሆነን በመሰለፋችን የጠላት ምኞት ከንቱ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የዘንድሮውን የገና በዓል ስናከብር በሽብርተኛው ቡድን ተፈናቅለው በመጠለያ ያሉ ዜጎቻችንን እያሰብን መሆን እንዳለበትም ነው ያመላከቱት።
አሁን ዐቢይ ጉዳያችን ሊሆን የሚችለው የሽብር ቡድኑ በአማራ እና በአፋር ክልል ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች መገንባት፣በጦርነቱ በግፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣የዘማች ቤተሰቦችን መንከባከብ እና መደገፍ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
መላው የክልሉ ህዝብ የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ ላበረከተው ሁለንተናዊ ድጋፍ ርዐሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ለመላው ዓለም በማስተዋወቅና ለሀገራችን ድምጽ በመሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዲያስፖራው መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ወደ ትውልድ ሀገሩ በመምጣት ላይ መሆኑን ገልጸው÷ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ አለኝታነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ በክልላችን ያለውን ፀጋ በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም ካጋጠሙን ፈተናዎች ይልቅ ከፊት ለፊታችን ያለውን የተስፋ ብርሀንን አሻግሮ ማየት ለበለጠ ልማት ያነሳሳናልም ነው ያሉት።
ሀገራችን ከውጭ በምናገኘው የስንዴ እርዳታ ተመጽዋች ሆና የምትቆይበት ምዕራፍ ሊያበቃ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
በቁጭት ከሰራን እና አንድነታችንን ካጠናከርን ሩቅ የመሰለን ህልም በእጃችን መዳፍ ስር እንደሚሆን መጠራጠር የለብንም ብለዋል።
በዓሉን ስናከብር የኮቪድ -19 በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ላይ ጥንቃቄ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት፣ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣የመተሳሰብ እና የአንድነት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!