በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግልፅ መረጃ እንዲኖረው እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግልፅ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ለዚህም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የተቀናጀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየሰራ መሆኑንም ኤጀንሲው ገልጿል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እንድሪስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ዳያስፖራው ብሄራዊ አንድነቱን ካሳየባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የግድቡ ጉዳይ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደየሚኖሩባቸው ሀገራት ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በአሜሪካው የኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ በበኩላቸው፥ ጊዜው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለብሄራዊ ጥቅማቸው የሚቆሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም የህዳሴው ግድብ የሁሉም ሃብትና መሆኑን ያነሳሉ፤ ጉዳዩን ለመንግስት ብቻ መተው ስህተት መሆኑን በመጥቀስ።
ታዛቢ ሆና ገብታ አደራዳሪ እና ህግ አርቃቂ ሆና ለቀረበችው አሜሪካ እና የዓለም ባንክ፥ መንግስት የሰጠውን ምላሽ አድንቀው አካሄዱ የግብፅ ሴራ የተሞላበት ነውም ብለዋል።
ምሁሩ አያይዘውም አሁን ግብጾች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ አቋም ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኢትዮጵያ በኩልም ለዚህ ሚዛን አስጠባቂ ግብረ መልስ መሰጠት አለበት ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው የህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባልም ነው ያሉት።
ይህን ስራ ደግሞ በሀገር ውስጥ ካሉ ምሁራን ጀምሮ ሁሉም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማከናወን እንደሚገባቸውም አውስተዋል።
ይህን በማድረግ በካይሮ የተሰራጨው የተዛባ ግንዛቤ ይስተካከላል የሚሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፥ ሂደቱ የአረቡ ዓለም እና የአፍሪካ ሃገራት ከእውነት ጎን እንዲቆሙ የማድረግ አቅም እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
በስላባት ማናዬ