Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የአሸናፊዋ ኢትዮጵያ ገፅታ ነው -ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብ ግንባታ ደረጃ እዚህ መድረስ ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የበለጠ እንድንተባበር የዲፕሎማሲ በራፍን እንደሚከፍት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

በዛሬው ዕለት ሦስተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በማብሰሪያው ላይ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ከመስጠት ያለፈ ትርጉም ያለው የአሸናፊዋ ኢትዮጵያ ገፅታ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንት ሣህርቅ ዘውዴ የተናገሩት።

ግድቡ ኃይል ከመስጠት ያለፈ ትርጉም ያለው ኢትዮጵያዊ ግድብ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከተባበርን መስራትና ማሳካት እንደምንችል ማሳያ፤ የአሸናፊዋ ኢትዮጵያ ገፅታም እንደሆነ ተናግረዋል።

እንዲሁም አንችልም እንዳንል፥ እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ዓባይ ላይ ግድብ መስራት ለብዙ ትውልዶች እንደ እሩቅ ህልም ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ኢትዮጵያውያን አማኞች በመሆናችን ተስፋ መሰነቅ የሚያቅተን አይደለንም ብለዋል፡፡

“ዓባይ ላይ ግድብ ለመስራት መታሰቡን እናውቃለን፤ ራዕይ ይዘው እኛ ባንችል ትውልድ ይሰራል ብለው የተናገሩ መሪም ነበሩ “ ብለዋል ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፡፡

በመቀጠልም ድፍረቱን ወደ ፊት ገፍተው ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ መሪም ነበሩ ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ዛሬ ደግሞ ተቋርጦ የነበረውን ስራ በማስቀጠል ኢትዮጵያን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኋላቀርንትና ከልመና ማላቀቅ አለብን ብለው ይህ ስራ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ ፤ ሁለት ተርባይን ሃይል እንዲያመነጭ ያደረጉና የግድቡ 3ኛው ዙር ውኃ ሙሌት እንዲጠናቀቅ ያደረጉ መሪ አይተናል” ብለዋል፡፡

በዚህም ህልማችን ዕውን ሆኗል፤ አሁን ፊታችንን ወደ ልማት የምናዞርበት ጊዜ ነው ፤ አሁንም ለግድቡ የምናደርገውን ድጋፍ እንቀጥል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.