ኢትዮጵያ የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ የብድር ሽግሽግን በተመለከተ ላሳለፈው ውሳኔ አድናቆቷን ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ የሀገሪቱን የብድር ሽግሽግን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ በበጎ ጎን እንደሚቀበለው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የአበዳሪዎች ሀገራት ኮሚቴ ኢትዮጵያ የእዳ ጫናን ለማቅለል ያቀረበችውን የብድር ሽግሽግ በተመለከተ ምክክር ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የእዳ ክፍያ ጥያቄውን ይፋ ካደረገ በኋላ አበዳሪ ኮሚቴው አራት ጊዜ ስብሰባ በማድረግ ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የምትችልበትን ስትራቴጂዎች ማቅረቡ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናን ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማቃለል ባዘጋጀችው ስትራቴጂ መሰረት አስፈላጊውን የፋይናንስ ዋስትና ለመስጠት ከሚቴው ለሚያደርገው ጥረት መንግስት አድናቆቱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አይ ኤም ኤፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍ አዳዲስ ፕሮግራሞችን በመንደፍ የሚያደርገውን ተሳትፎ አድንቋል ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴውም ኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ሂደት ጫና ሳይበረታባት የሚጠበቅባትን የብድር ግዴታዎች መወጣት እንድትችል ለሚያደርገው የብድር ሽግሽግ አድናቆቱን መንግስት ገልጿል።