በበልግና ክረምት ዝናብ ምክንያት የሚፈጠረውን የጎርፍ ውሃ ለበጋ ግብርና ሥራዎች ለማዋል እየተሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበልግና ክረምት ዝናብ ምክንያት የሚፈጠረውን የጎርፍ ውሃ ለበጋ ግብርና ሥራዎች ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር) ገለጹ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር) የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር እና ዳሰነች ወረዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የጎርፍ መከላከል ሥራን ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ዓላማም በጅንካ ከተማ እና በሐመር ወረዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን እንዲሁም በዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ እያስከተለ ያለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በ119 ሚሊየን ብር እየተከናወኑ የሚገኙ የወንዝ አመራር ሥራዎችን ለመገምገም ነው።
ሚኒስትሩ በደቡብ ኦሞ ዞን እስከ ሶማሌ ክልል ባለው ቀጣና እየደረሰ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የኦሞ ወንዝን ከመጠን ያለፈ ፍሰት በማመጣጠን የተወሰነውን የውሃ ክፍል አቅጣጫ ቀይሮ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዲውል እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በጎርፍ የተያዘውን የመሬት ክፍል ነፃ በማድረግ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ተመልሰው በመስኖ እና ለተያያዥ የልማት ሥራዎች እንዲሰማሩ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የኦሞ፣ የጊቤ እና አዋሽ ተፋሰስ ወንዞች የሚያስከትሉትን የጎርፍ አደጋ ምላሽ በመስጠት በበጋ ወራት የሚከሰትን የድርቅ አደጋ መከላከል የሚያስችል የመስኖና የመጠጥ ውሃ በመያዝ ኃብት ማመንጨት የሚቻልበት ሥርዓት እንደሚፈጠርም አንስተዋል።
ዘላቂነት ያለው የትላልቅ ወንዞች አመራር ሥርዓት በማበጀት ጎርፍ አደጋ መሆኑ ቀርቶ ለዓሳ እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች እንዲውል በማድረግ ለዜጎች ጥቅም እንዲሰጥ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።