Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ 28 ነጥብ 2 በመቶው ብቻ ለአርሶ አደሮች መቅረቡ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 28 ነጥብ 2 በመቶው ብቻ ለአርሶ አደሮች መቅረቡ ተገለፀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ እንደገለጸው ÷ በክልሉ 9 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋል።

የቢሮው ምክትል እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ እንደገለፁት 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ የገባ ሲሆን ÷ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታሉ ብቻ ነው ለአርሶ አደሮች የደረሰው።

አርሶ አደሮችም በወቅቱ ግብዓት ስላልደረሳቸው የዘር ወቅት እንዳያልፋቸው ስጋታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

እጥረቱን ለመቅረፍ ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ በሪሶ ፈይሳ ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በአቅርቦቱ ላይ ችግር እንደፈጠሩም ነው የጠቀሱት።

ማደበሪያን ለሌላ አገልግሎት ሲያውሉ የተገኙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በአዳማ ፣በዱከምና ደብረ ዘይት ማዳበሪያን በፋብሪካዎች ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ሲጠቀሙ የተገኙ ፋብሪካዎችም መታሸጋቸውን አቶ በሪሶ አብራርተዋል።

በሕገወጥ ሽያጭ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረገ የሚገልጹት ሃላፊው ማዳበሪያን ከመንግሥትና ከማሕበራት ውጪ የሚያሳራጩትን በጋራ መከላከል እንዲቻል ሕብረተሰቡም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

በሲሳይ ዱላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.