ራሚዝ አላክባሮቭን የተመድ በኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሆነው ተሾሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ራሚዝ አላክባሮቭን (ዶ/ር) የድርጅቱ በኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ አድርገው ሾሙ፡፡
አላክባሮቭ(ዶ/ር) በአስፈፃሚ አመራር፣ በስትራቴጂክ እቅድ እና ፖሊሲ ማውጣት፣ በልማት ፕሮግራም እና አስተዳደር እና በሰብአዊ ምላሽ የ28 ዓመታት ልምድ ያላቸው ናቸው።
የአዘርባጃኑ ዜጋ አላክባሮቭ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት በአፍጋኒስታን የተመድ የእርዳታ ተልዕኮ ምክትል ልዩ ተወካይ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ሆነው አገልግለዋል።
በተጨማሪም ተሿሚው በተመድ የስነ ህዝብ ፈንድ ውስጥ በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ ያገለገሉ ሲሆን ፥ በድርጅቱ የአስተዳደር እና የማሻሻያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና በኒው ዮርክ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።
በተመሳሳይ በሄይቲ የሀገር ተወካይ፣ የዓረብ ሀገራት ቀጣና ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና በደቡብ ሱዳን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ከነዚህ ኃላፊነቶች በፊትም በተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ በሚደግፉ የአረብ ሀገራት፣ በምስራቅ አውሮፓ እና በመካከለኛው እስያ ሀገራትን ጨምሮ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በኢራቅ የፕሮግራም ባለሙያ እና በአፍጋኒስታን፣ ፍልስጤም እና ታላላቅ ሐይቆች የሰብዓዊ ምላሽ ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል።
ከፈረንጆቹ 1992 እስከ 1995 በአዘርባጃን ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እና የህክምና ባለሙያ እንደነበሩም ነው ተመድ በማህበራዊ ትስስር ገጹ የገለጸው፡፡
አላክባሮቭ (ዶ/ር) የሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ እና ፒኤች ዲግሪ ከአዘርባጃን ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ማስተር ኦፍ አርት ከቦስተን፣ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ ከሚገኘው ፍሌቸር የህግ እና የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት አግኝተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!