Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ወደ ኋላ የማይልና በቁርጠኝነት የሚሰራበት ጉዳይ ነው- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህ ረገድ የተጀመረው ጥረት የስርዓተ ትምህርት ለውጥን ጨምሮ በርካታ አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሁሉም የትምህርት ደረጃ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

የስርዓተ ትምህርት ለውጡን ተከትሎ ተፈጥሮ የነበረውን የመጽሃፍ እጥረት ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን በማስታወስ ÷እስከ ህዳር መጨረሻ ለበርካታ ተማሪዎች መጽሃፍ ተደራሽ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል “ትውልድ ለልማት” በሚል በተጀመረው ንቅናቄ ጠንካራ የህብረተሰብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ጠቅሰው በዘመቻው የላቀ ውጤት ተመዝግቧል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ርዕሳነ መምህራንን ከፖለቲካ ፍላጎት በፀዳ መልኩ በችሎታቸው ቦታ እንዲይዙ የተሄደበት ርቀትም አበረታች እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ዙሪያ ብዙ ለውጦች እየተከናወኑ እንደሚገኙ በማስታወስ ለ4 ሺህ መምህራን አንድ ዓመት የፈጀ የተግባር ትምህርት መሰጠቱንም በአብነት ጠቅሰዋል።

የመውጫ ፈተና መሰጠት መጀመሩንና፣ የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ወጥ እንዲሆን መደረጉንም ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ለውጥ በምንም አይነት ሁኔታ ወደ ኋላ የማይልና በቁርጠኝነት የሚሰራበት ጉዳይ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.