በሩብ ዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ የኦንላይን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የንግድ ፈቃድን ጨምሮ ተያያዥ አገልግሎቶችን በኦንላይን ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡
የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጻም መመዝገቡ ነው የተገለጸው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ÷ በሩብ ዓመቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ የተሻለ ስራ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የነዳጅ ግብይት ስርዓት ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ከነዳጅ ግዢ ትዕዛዝ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ማጓጓዝ እንዲሁም የስርጭት ሂደቱን በዲጂታል ስርዓት የመቆጣጠር ስራ በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ መጀመሩን ነው የተናገሩት።
የንግድ ስርዓቱን በማዘመን ረገድም በሩብ ዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የንግድ ፈቃድን ጨምሮ ተያያዥ አገልግሎቶችን በኦንላይን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሩብ ዓመቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን በኦንላይን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ የቴክኖሎጂ ዘርፍ መነሻ ሃሳቦች (ስታርታፖችን) በመደገፍ ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፥ ይህም በዲጂታል ስርዓት አማካኝነት ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ አስረድተዋል።
ለአብነም የጫት ወጪንግድ ላይ በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የጫት ወጪንግድ መጠን በእጥፍ እንዳደገ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡