ከአርሶ አደሮች በህገ ወጥ መንገድ ተነጥቆ ተይዞ የነበረ 460 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለአርሶ አደሮቹ ተመለሰ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአርሶ አደሮች በህገወጥ መንገድ ተነጥቆ ተይዞ የነበረ 460 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለአርሶ አደሮቹ መመለሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
በህገወጥ መልኩ ከአርሶ አደሮች የተወሰደው መሬት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ባደረጉት ማጣራት ተመላሽ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ቦታቸውን መልሰው የተረከቡት አርሶ አደሮቹ ተታለው ቦታቸው የተወሰደባቸው መሆኑን ገልጸው መልሰው ማግኘት በመቻላቸው ምስጋናቸው መግለፃቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሮቹ በቦታው ላይ የከተማ ግብርና እንዲተገብሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገልጸዋል።
በቀጣይም ከአርሶ አደሮች ያለአግባብ የተወሰዱ መሬቶች ላይ ማጣራት እንደሚደረግና ለአርሶ አደሮች ተመላሽ እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችም በዚህ ዙሪያ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።