የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ ከ1 ሺህ 880 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአስሩም ክፍለ ከተሞች ባደረገው ድንገተኛ የምሽት ቁጥጥር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 1 ሺህ 887 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው የተገኙ 641 ሰዎች በገንዘብና በእስራት መቀጣታቸውንም አስታውቋል።
እስከ ዛሬ ድረስም አራት እና ከአራት በላይ በመሆን በተለያዩ ቦታዎች መጠጥ ሲጠጡ፣ በቁማር ቤቶች ቁማር ሲጫወቱ፣ በቡና ጠጡ ቤቶች ቡና ሲጠጡ እንዲሁም በአንድ ስፍራ ተሰባስበው ጫት ሲቅሙ እና ሺሻ ሲያጨሱ በተገኙ 1 ሺህ 523 ሰዎች ላይ ምርማራና ማጣራት ማድረጉን ገልጿል።
ከዚህ ውስጥ 641 ሰዎች በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው 74ቱ ከ15 ቀን እስከ 3 ወር በሚደርስ እስራት እንዲሁም 556 ደግሞ እስከ 20 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደተቀጡም ነው ያስታወቀው።
ኮሚሽኑ አሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ከመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲጭኑ የወጣውን መመሪያ በጣሱ፣ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ በተገኙ፣ ኮድ 2 ሆነው ከተፈቀደላቸው ቀን ውጭ ሲንቀሳቀሱ እና በባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ላይ ሰው አሳፍረው በተገኙ 5 ሺህ 360 አሽከርካሪዎች በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉንም ጠቅሷል።
ህዝብ በስፋት በሚገኝባቸው የንግድ ቦታዎች፣ አደባባዮችና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ርቀታቸውን በማይጠብቁ በተለይ ደግሞ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም ሲኖርባቸው በማይጠቀሙ ግለሰቦች በጥቅሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚተላለፉ ግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥሩን እንደሚያጠናክርም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።