Fana: At a Speed of Life!

ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 23 ግለሰቦች ክርክር በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እነ ወንደሰን አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ 23 ተከሳሾች በአካል ሳይቀርቡ ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው ክርክራችንውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲያደርጉ ጠየቀ።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከስድስት ወራት በፊት በአማራ ክልል ተከስቷል ከተባለው ሁከትና አመጽ ጋር ተያይዞ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) እና መስከረም አበራን ጨምሮ የ51 ግለሰቦችን ስም ዝርዝር አካትቶ በየተሳትፎ ደረጃቸው የሽብር ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ከተከሳሾቹ መካከልም 23ቱ የተከሰሱበት ድንጋጌ የዋስትና መብት የሚገድብ መሆኑን ተከትሎ በማረሚያ ቤት ሆነው ችሎት እየቀረቡ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በዛሬው ቀጠሮ የግራ ቀኝ ክርክር ለማድረግ ችሎቱ ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም አንድ ተከሳሽ ተሟልቶ አለመቅረቡን ተከትሎ በተሟላ መልኩ በቀጣይ ክርክር ለማካሄድ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹ በአካል ሳይቀርቡ ካሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው ክርክራቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲያደርጉ እንዲታዘዝለት ለችሎቱ አመልክቷል።

ባቀረበው ማመልከቻም ተከሳሾቹ ችሎት መቅረብ ከጀመሩ አንስቶ በእያንዳንዱ ቀጠሮ ዝግጅት በማድረግ፣ ከችሎት ሲወጡ በኅብረትና በአንድነት ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ፣ የተለያዩ ጩኸቶችን በማሰማት የሥራ አካባቢን እያወኩ ነው የሚሉ ምክንያቶቹን ጠቅሷል፡፡

ማንኛውም ግለሰብ ተከሶ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የፍርድ ቤት አካባቢ ሥርዓትን በማክበር ጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ ከፍርድ ቤት ፍትሕን መጠበቅ ይገባዋል ያለው ዐቃቤ ሕግ÷ ተከሳሾቹ ከዚህ በተቃራኒ ሆነው ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት በማምጣት የፍትሕ ሥርዓቱን እያወኩ ነው ብሏል፡፡

የተከሳሾቹ ድርጊት በፍርድ ቤት በዝምታ በመታለፉም ዛሬ ፍርድ ቤት ፊትለፊት ቆመው ፍትሕ የሚጠብቁ እና ፍርድ ቤት ሆነው ድርጊቱን የሚያዩ ሁሉ ፍርድ ቤት ውስጥ መጮህና መረበሽ ይቻላል የሚል ግንዛቤ የሚሰጥ ድርጊት ነውም ብሏል ዐቃቤ ሕግ፡፡

ድርጊቱ በተገልጋይ መስተንግዶ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳርፍም አመላክቷል፡፡

ተከሳሾች እንደማንኛውም በሕግ ቁጥጥር ስር እንዳለ ሰው ሕግ ማክበር እንዳለባቸው ጠቅሶ ማረሚያ ቤት በትዕግስት እየተከታተላቸው መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ስለሆነም ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ክርክሩን እንዲያካሂዱ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ሲል ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎትም በቀረበው ማመልከቻ ላይ በተከሳሾቹ ጠበቆች በኩል አስተያየት እንዲሰጥበት በሚል ውጤቱን ለመጠባበቅ ለመጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.