አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘርፉ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዘርፉ የተሰጠውን መልካም ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎን ለጎን ከሚካሄዱ መርሐ ግብሮች መካከል “የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ሁኔታዎች ” በሚል የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ የተሳተፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እና ሊፈቱ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ፥ አምራች ዘርፉን መደገፍ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።
የአምራች ዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት እና ወጪ ምርቶችን በማበረታታት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም ነው የገለጹት።
የማዕድን ሚኒስትሩ ሐብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) በበኩላቸው ፥ የዘርፉን ተግዳሮት ለመፍታት ተገቢውን ምክክር ማድረግና አስፈጻሚ አካላትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚታዩ አመለካከቶችን በማስተካከል የዘርፉን አቅም ማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር) ፥ ባንኩ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በዝቅተኛ የወለድ መጠን የዘርፉን ተዋንያን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ አምራች ዘርፉን እየደጎመ የሚገኝ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር)፥ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት ፥ የዘርፉ ተዋንያን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ መመልከት እንዳለባቸው ገልጸው ፥ በሚጠበቀው ልክ መሥራት አለመቻል ዘርፉን በዋናነት እየፈተነው እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ለማስተካከል ወደ ውስጥ ማየት እንደሚገባም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡