የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወልቂጤ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነገ በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት ለመምራት ወደ ከተማዋ የገቡት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ጌታሁን አብዲሳ በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡
በምልከታቸውም የወልቂጤ ከተማ አሥተዳደር የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የግል የኢንቨስትመንቶችን፣ ከወረቀት ነጻ አገልግሎትን እና ዘመናዊ የቄራ ግንባታን መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ ነገ በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት እንደሚመሩ መገለጹን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ነገ የሚካሄደውን ሕዝባዊ ውይይት ለመምራት ሆሳዕና ገብተዋል፡፡