የአፍሪካን ሚዛን በማስጠበቅ አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር የሰነቀው ፐልስ ኦፍ አፍሪካ …
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ የአፍሪካን ሚዛን በማስጠበቅ አህጉራዊ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካ መልክና ድምፅ የሚስተጋባበት ሚዲያ ነው፡፡
ለአፍሪካዊያን የተበረከተ አህጉራዊ ትርክት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ጠቁመው ÷ መላው አፍሪካዊያን ድምጻቸውን እና መልካቸውን የሚመለከቱበት ነው ብለዋል፡፡
ዜና፣ ወቅታዊና የመዝናኛ ሥራዎችን የሚከውነው ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ÷ በመረጃ ደረጃ መሪ ማዕከል ሆኖ ለመዝለቅ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካን ድምጾች የሚያጎላ እና አህጉራዊ ስኬቶችን ለመላው ዓለም የሚያሳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ሚዲያው የኢትዮጵያን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ የአፍሪካን መልካም ነገሮች አጉልቶ ለዓለም ከማሳየት ረገድ በርካታ ሥራዎችን ያከናውናል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ በእንግሊዝኛና ዓረብኛ ቋንቋዎች ሥርጭት መጀመሩን ጠቅሰው ÷ በቀጣይ ጥናቶች ተደርገው ብዙ ተደራሽነት ባላቸው ሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የኢትዮጵያን መሻትና የአፍሪካን ልዕልና መዳረሻው ያደረገ ሚዲያ እንደሆነ አውስተው ÷ በትርክት ረገድ የአፍሪካን ሚዛን በማስጠበቅ አህጉራዊ ትስስር የሚገነባበት ነው ብለዋል፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሥርጭቱን በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ሚዲያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የአፍሪካን እይታና ትርክት የሚያንፀባርቅ የአህጉራዊ ሚዲያን አስፈላጊነት አስመልክተው ያቀረቡትን ጥሪ በመመርኮዝ የተመሠረተ ነው።
በወንድማገኝ ጸጋዬ