ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት ዘመኑን በዋጀ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በውሃ ሀብትና በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ሀብት ዘመኑን በዋጀ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ስራ እያከናወነች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴሩ በውሃ እና ኢነርጂ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዶች ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችል ውይይት ከዘርፉ ተዋናዮች ብሎም አጋር አካላት ጋር አካሂዷል።
በመድረኩ ለተሳታፊዎቹ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የተዘጋጁ ረቂቅ ፖሊሲዎች አጠቃላይ ይዘት እና እንደ ሀገር የሚኖራቸውን ፋይዳ በተመለከተ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብት እንዲሁም ከኢነርጂው ዘርፍ እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባትን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስገኘትና ዘርፉን በተጠናከረ መንገድ ለመምራት ፖሊሲ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም እውን ለማድረግ የውሃና የኢነርጂ ፖሊሲዎችን ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸው÷ በኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
ረቂቅ ፖሊሲዎቹ የውሃ ሀብትን ብሎም ኢነርጂን በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋልና ለማስተዳደር እንዲሁም በሀገሪቱ ፍትሃዊ ተደራሽነት በሚያረጋግጡ መልኩ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በውሃ እና በኢነርጂ መስኮች ላይ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እውን ለማድረግ መንግስት በሚሰራው ስራ ብቻ ዘርፉን ማጎልበት አዳጋች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ የወጡ ረቂቅ ፖሊሲዎች ዘርፉ የግሉን ባለሀብቶች የሚሳተፉበትን አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በኢነርጂው ዘርፍ ላይ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተደራሽነት አኳያ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የዘርፉ ተዋናዮች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡