ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይሆን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይሆን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን መርቀው ለአገልግለት ማብቃታቸውን በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም እኩል የማዘመን፣ የማስዋብና በልማት የማሸጋገር ሀገራዊ ራዕይ በተግባር የታየበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአንድ ወር የግንባታ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ሞዴል መንደሩ በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የቆየውን የጤና ጣቢያ፣ የመብራትና የውኃ አገልግሎት ጥያቄ በተግባር የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የአካባቢውን ቁሳቁስ ከዘመናዊ መሃንዲስ ዕውቀት በማሰናሰል በአካባቢው በሚታወቀው የ”ደቢያት” የትብብር ባህል ደግሞ አርሶ አደሩን ቀጥታ በማሳተፍ እጅግ ዘመናዊ ቤቶች መገንባታቸውን አመላክተዋል።
በፕሮጀክቱ የሰዎች መኖሪያን ከእንስሳት መጠለያ በመለየት ለጤናማና ለሥልጡን አኗኗር መሠረት ጥለናልም ነው ያሉት።
ዙሪያውን በተቀናጀ የሌማት ትሩፋት የታጀበው የገጠር ኮሪደሩ አርሶ አደሩን የዘመናዊነትና የምርታማነት ባለቤት የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።
ዛሬ ጎንደርም ሆነች ድፍን ሀገራችን ከተማው ብቻ ሳይሆን ገጠሩም እኩል እየተዋበ፣ በልማት እየተገነባና በዕድገት ፍኖት ላይ በጽኑ መሠረት እየተራመደ ይገኛል ብለዋል።
ይህ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የማሸጋገር ትልቁ ማሳያችን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።