ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክር ረቂቅ አጀንዳዎችን ለሲቪክ ተቋማትና ማህበራት አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ረቂቅ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ለሆኑ ሲቪክ ተቋማትና ማህበራት አቅርቦ ግብዓት አሰባስቧል፡፡
ዛሬ በተካሄደው መድረክ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ ሲቪክ ተቋማትና ማህበራት በምክክሩ ሒደት ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው።
ኮሚሽኑ ከተቋማቱ ጋር መሥራቱ የገለልተኝነት እሴትን ለማስጠበቅ አስችሎታልም ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የምክክር ጉባኤው ከመከናወኑ በፊት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አጀንዳዎችን አሳውቆ ምክረ ሀሳብ ለማሰባሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ የኮሚሽኑን የአራት ዓመታት ሒደት የሚያስቃኝ ገለጻ አድርገው፤ ሲቪክ ማኅበራትና ተቋማት በቀጣይ ለሚከናወነው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጀመሩትን ጉልህ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተቀረጹ ረቂቅ የአጀንዳ ሀሳቦችን አስመልከቶ ገለጻ ያደረጉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ አጀንዳዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ የረቂቅ ሒደት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ግብዓት በስፋት ተካትቶበት እንደሚዳብርም ማረጋገጣቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
የሚቀረጹት አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6 መሠረት እንደሆነ ያስረዱት ደግሞ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ናቸው።
በአዋጁ መሠረትም አጀንዳ የሚቀረጽበት መስፈርት ለሀገራዊ መግባባትና ሰላም የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚታዩት ሀገርን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነር መላኩ፤ ሲቪክ ማህበራትና ተቋማት ለሀገራዊ ጉባኤው ስኬት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ዕድሮች ጥምረት፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን፣ ኢትዮጵያንስ ፎር ኢንክሉሲቭ ዲያሎግ፣ ትምራን እና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ተሳትፈዋል፡፡