Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የካዳስተር መተግበሪያ ሶፍትዌር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህጋዊ የካዳስተር ስርዓትን ቀልጣፋና ወጥ በሆነ መልኩ መተግበር የሚያስችል የመተግበሪያ ሶፍትዌር በአዳማ እየተካሄደ ባለው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተር ጉባኤ ላይ ተመርቋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተሰራው ይህ ሶፍት ዌር የዜጎች የይዞታ መብት እንዲረጋገጥና በዘርፉ የሚታየውን ውስብስብ የሆነ አሰራር ግልፅ፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመልክቷል።
የመተግበሪያ ሶፍትዌሩን የመረቁት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የስራ ሀላፊ የሆኑ ሴት ሚኒስትሮች የመተግበሪያው እውን መሆን ከመሬትና ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ለሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና እንግልቶችን ለማስቀረት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ወደተግባር መግባት ይኖርበታል ሲሉ ገልፀዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ የመሬት ምዝገባ ጉዳይ ህብረተሰቡን ያማረረ ለኪራይ ሰብሳቢነት ያጋለጠና ስንቸገርበት የቆየ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን ሊፈታ የሚችል ሶፍትዌር ተሰርቶ ይፋ መደረጉ ትልቅ እፎይታ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፥ ጉዳዩ ውስብስብና ብዙ ህብረተሰብና መንግስትም ጭምር ሲቸገርበት የቆየ፣ አሰልቺ የሆነ ቢሮክራሲ ያለበት፣ ሀብትንም ያባከነና በተጨባጭ ለውጥ ያልመጣበት እንደነበር ገልፀው የመተግበሪያው እውን መሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስትም መተግበሪያውን ወደመሬት ለማውረድና ለመተግበር ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋም፥ መተግበሪያው ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መሬትን እንደ ትልቅ ሀብት እንዲታይ የሚያደርግ ፣ተገማች አሰራርን የሚዘረጋና ህጋዊ ማረጋገጫ መስጠት የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት ወደተግባር ገብቶ ለማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፥ ሲስተሙን ከተሞች ለማስጀመር ዝግጅት እንዲያደርጉና በፍጥነትም ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ስለአሰራሩ ማወቅ እንዲጀምርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩ መናገራቸውንም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.