ዓለም አቀፉ የትምህርት ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በዓለም አቀፉ የትምህርት ጉባኤ ላይ በበይነ መረብ እየተሳተፉ ነው፡፡
ጉባኤው በጋና፣ የኖርዌይ፣ እንግሊዝ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) በ ጋራ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ጉባኤው ስለ ትምህርት ፋይናንስ፣ በኮቪድ 19 ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ስለመክፈት፣ የአካቶ ትምህርት፣ የመማር ማስተማር ሂደትና እና በዲጅታል ትምህርት ዙሪያ ትኩረቱን አድርጓል።
በጉባኤው ላይ በ2021 የዓለም የትምህርት የትኩረት መስክ ምን መምሰል እንዳለበት ቀጣይ አቅጣጫና ውሳኔ እንደሚተላለፍ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የትምህርት ሚኒስትሮች እና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጭዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡