ምርጫው በክልሉ የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቅንጀት እየሠራን ነው- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የድጋሚ የምርጫ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ምርጫው ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተለየ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽንና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስተወቁ።
ምርጫው የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጀት ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱላዚም መሃመድ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ምርጫው የማይካሄድ እና ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ተነጥሎ እንዲራዘም የሚደረግ ከሆነ በክልሉ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ መዋቅር አይኖርም በሚል ቅስቀሳ በህብረተሰቡ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር እና ግጭት ለማስነሳት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎችና ጥቆማዎች መኖራቸውንም ነው ኮሚሽነር አብዱላዚም የጠቁሙት፡፡
የክልሉ ህዝቦች የእነዚህን ኃይሎች የጥፋት ሴራ በሚገባ በመገንዘብ ከኮሚሽኑ እና ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ ዕቅዳቸው እንዳይሳካ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኮሚሽነሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ሰይድ ባበክር በበኩላቸው ፥ የመንግስት ስልጣን መያዝ የሚቻለው በህዝብ ምርጫ ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ ከዚህ ውጪ ስልጣን በኃይል ለመያዝ መሞከር ኢ- ህገ መንግስታዊ እና ከምርጫ ህጉ ውጪ የሆነ አስተሳሰብና ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ አካላት ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው በመንቀሳቀስ ከእኩይ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው ተቆጥበው ለህግ ተገዥ በመሆን ለጋራ ሰላም መስፈን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታውን አስመልክቶ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽንና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጋራ የተሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ከ6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ሀገራዊና ክልላዊ ክስተቶችን ተከትሎ በተለይም በክልላችን መተከልና ካማሽ ዞኖች በነበረው የፀጥታ ችግር እንዲሁም በአሶሳ ዞን መገሌና ሆሃ ምርጫ ክልሎች በተከሰተ የድምፅ መስጫ ካርድ እጥረት ምክንያት ምርጫው ሳይካሄድ መቅረቱ እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሰረት እንደሚካሄድ ተወስኖ የነበረ መሆኑን ኮሚሽነር አብዱላዚም መሃመድ አስታውሰዋል፡፡
በዚሁም መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የድጋሚ የምርጫ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ምርጫው በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያገኘ ፣ ነፃ፣ ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተለየ ትኩረት ሰጥተን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጀት ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
በአንፃሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ምርጫው የማይካሄድ እና ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ተነጥሎ እንዲራዘም የሚደረግ ከሆነ በክልሉ መንግስትም ሆነ መንግስታዊ መዋቅር አይኖርም በሚል ቅስቀሳ በህብረተሰቡ ውስጥ ሁከት ለመፍጠር እና ግጭት ለማስነሳት በዝግጅት ላይ ስለመሆናቸው የሚያመላክቱ መረጃዎችና ጥቆማዎች መድረሳቸውን ኮሚሽነር አብዱላዚም መሃመድ ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ አካላት ከዚህ የጥፋትና የተንኮል ሴራቸው እንዲታቀቡ ኮሚሽነሩ በጥብቅ አሳስበው ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠረው ማናቸውም ዓይነት የፀጥታ ችግር ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስዱ ከመሆኑ ባሻገር የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የአካባቢውን ሠላም ለማስከበር ሲባል ኮሚሽኑ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ኮሚሽነሩ አሳውቀዋል፡፡
መላ የክልላችን ህዝቦች የእነዚህን ኃይሎች የጥፋት ሴራ በሚገባ በመገንዘብ ከኮሚሽኑ እና ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመሰለፍ ዕቅዳቸው እንዳይሳካ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንድወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ሰይድ ባበክር የመንግስት ስልጣን መያዝ የሚቻለው በህዝብ ምርጫ ብቻ መሆኑን አስታውሰው ከዚህ ውጪ ስልጣን በኃይል ለመያዝ መሞከር ኢ- ህገ መንግስታዊ እና ከምርጫ ህጉ ውጪ የሆነ አስተሳሰብና ተግባር መሆኑን ገልፀው እነዚህ አካላት ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው በመንቀሳቀስ ለህዝቡ ደህንነት መጠበቅ ሲሉ ከእኩይ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው ተቆጥበው ለህግ ተገዥ በመሆን ለጋራ ሰላም መስፈን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለህዝባችን ደህንነት መጠበቅና ለአካባቢያችን ሠላም መረጋገጥ ዘወትር ተግተን እንሰራለን!!
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኪሚሽን እና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም
አሶሳ፤
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!


0
People Reached
23
Engagements
Boost Post
23