የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራ በሚፈጥረው የሥራ ዕድል ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ…
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው ለሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት በፈጠረው የሥራ ዕድል ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል አሉ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት÷ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው ለሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት የፈጠረውን ዕድል ለዜጎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ ባለፉት 6 ወራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን በብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው በተፈጠረ የሥራ እድል በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ቀሪው የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርቀት የተፈጠረ የሥራ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ከልየታ እስከ ሥራ ስምሪት ድረስ ያለው ተግባር የተከናወነው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ አጠቃቀምን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ለዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት መረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።