Fana: At a Speed of Life!

በካሳጊታ በከባድ መሳሪያ ተመተው የወደቁ ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በካሳጊታ በከባድ መሳሪያ ተመተው የወደቁ ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመር ጥገና የቴክኒክ ድጋፍ ኃላፊ ገልፀዋል፡፡

ኃላፊው አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለፁት÷ የደረሱ ጉዳቶችን በመለየትና በፍጥነት መልሶ በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በተቋሙ ዘጠኙም ሪጅኖች ያሉ የጥገና ባለሙያዎች በቅንጅት በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

የጥገና ቡድኑ ሥራውን ለማቀላጠፍ በሦስት አቅጣጫዎች – በጋሸና፣ በኮምቦልቻ እና በሚሌ መስመሮች ተከፋፍሎ እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በኮምቦልቻ መስመር ጥገናውን እያከናወነ ያለው ቡድን ባከናወናቸው የመልሶ ጥገና ሥራዎች ከሸዋ ሮቢት እስከ ደሴ ያሉ ከተሞች እንዲሁም ወደ አቀስታ መስመር ያሉ ከተሞች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡

በሚሌ በኩል ያለውን የጥገና ሥራ የሚያስተባብሩት የምሥራቅ ሪጅን ትራንስሚሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ በበኩላቸው ÷ ከካሳጊታ እስከ ኤሊውሃ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው መስመር ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና መስመሩን በአብዛኛው እንደአዲስ የመዘርጋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በካሳጊታ በከባድ መሳሪያ ተመተው የወደቁ ሶስት ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ መጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡

ከኮምቦልቻ ሠመራ የሚሔደውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የጥገና ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በአራት ቡድኖች ተከፋፍሎ ሁሉም ተናቦ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጥገና ቡድኑ ሥራውን በፍጥነት ለማጠናቀቅና በበርካታ የአፋር ከተሞች የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በትጋት እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.