የጭፍራ ጤና ጣቢያን አገልግሎት ለማስጀመር ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሲ ረሱ ዞን ጭፍራ ወረዳ የጭፍራ ጤና ጣቢያን መልሶ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አወል አሊ ገልጸዋል።
ከ19 ዓመት በላይ አገልግሎት የሰጠው የጭፍራ ጤና ጣቢያ ከ39 ሺህ 900 በላይ ለሚሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ጤና ጣቢያው በሥሩ ለሚገኙ 7 ጤና ኬላዎች “እንደ ሪፈራል” በማገልገል ለታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ኃላፊው ጠቁመው ፥ ይህም አገልግሎቱ እንደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሆኖ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡
ጤና ጣቢያው ለ19 ዓመታት ያደራጀውን የሕክምና መሣሪያ እና ቁሳቁስ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአካባቢው በወረራ በቆየበት ጊዜ ከፍተኛ ውድመት እና ስርቆት ፈጽሞበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጳውሎስ ሆስፒታል ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ጤና ጣቢያው ከነበረው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሃላፊነቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ እና የሕክምና ቁሶችም ደረጀ በደረጃ እየተሟሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የወደሙ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን የማስጠገን ስራ በጳውሎስ ሆስፒታል የተከናወነ ሲሆን፥ የጀነሬተር እና ሌሎች የሕክምና ማሽኖችን ለመጠገን እና አዲስ ለማስገባት ሆስፒታሉ ጥናት አድርጎ ማጠናቀቁም ተገልጿል።
የጭፍራ ጤና ጣቢያ አሁን ላይ ማዋለድን ጨምሮ የእናቶችና ህፃናት ሕክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስጀመር የመብራትና ውሃ አቅርቦት በፍጥነት እንደሚያስፈልጉት በስፍራው የሚገኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሚዲያ ቡድን ተመልክቷል።
በፍሬህይወት ሰፊው እና አልማዝ መኮንን
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!