Fana: At a Speed of Life!

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰን የኢትዮጵያን ገጽታ ሲያጠለሹ የነበሩ ሀይሎችን አሳፍሯል

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑ የኢትዮጵያን ገጽታ ሲያጠለሹ ለነበሩ ሀይሎችን ያሳፈረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፥ የመጀመሪያው በህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በጥር ወይም በየካቲት ወር ላይ ይካሄዳል ።
ሁለተኛው ደግሞ የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር በሆነችው ሀገር አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው።
በአፍሪካ ህብረት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የአሁኑ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ይህ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ ብዙ ፈተናዎች ታልፈዋል የሚሉት አምባሳደር ዲና፥ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው ጉባኤው በአዲስ አበባ ዘንድሮ እንዲካሄድ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ይላሉ።
ይህ ጉባኤ ከአህጉራዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች እስከ አጀንዳ 2063 አፈጻጸም በርካታ ጉዳዮች ውይይት እንደሚደረግበት ነው የሚጠበቀው።
ከዚያ ባሻገርም የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም ምርጫዎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በኮቪድ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የፊት ለፊት ስብሰባ አልተደረገም።
ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ኮቪድ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ህግ ለማስከበር በተወሰዱ ገንቢ እርምጃዎች የተከፉ አንዳንድ ወገኖች ስውር እጆች በመኖራቸው ጫናዎች ነበሩ ።
እነዚህን ለመሻገር በኢትዮጵያ በኩል ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በተለያዩ እርከኖች ውስጥ የሚገኙ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በስራ ላይ ያሉ ወገኖች ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፥ የአፍሪካ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ በመረዳት፣ ለኢትዮጵያውያንም ወገንተኝነትን ለመግለጽ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለመቆም ባላቸው ፍላጎትና ስሜት አዲስ አበባ በአካል እንዲደረግ ተወስኗል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው የሚሆነው ብለዋል።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ፣ ሉዓላዊነትና ሰላም የምታደርገውና ስታደርግ የኖረችውን ተጋድሎ በሚገባ ስለሚረዱ ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ጉባኤው በአካል በአዲስ አበባ እንዲሆን ወስነዋልም ነው ያሉት።
ምንም እንኳን ስውር እጆች ይህንን ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ቢኖርም እነዛን እጆች አፍሪካውያን በመቀስ ቆርጠዋቸዋል ነው ያሉት።
ይህም አጋጣሚ የኢትዮጵያን ገጽታ ሲያጠለሹ የነበሩ ሀይሎች ያፈሩበት ሲሆን፥ የሀገራችንን መልካም ገጽታ ግንባታ ላይ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እኛም ፈተናዎቹን ሁሉ አልፈን ጉባኤውን ማስተናገዳችን አዲስ አበባ የተረጋጋች፣ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት መዲና መሆኗን ያሳያል ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ በርካታ እንግዶች ስለሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።
መንግስት ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባዔው የተሳካ እንዲሆንም ሁሉም በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳን የማስተናገድ ልምዱ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።
ከሁሉም በላይ በዚህ ከባድ ጊዜ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እኛን ብለው ስለሚመጡ በአፍሪካዊ ስሜት ማስተናገድ ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.