Fana: At a Speed of Life!

የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ሰላምና ደህንነትን ጨምሮ በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በዋናነት ሰላምና ደህንነት፣ ቀጣናዊ ትስስርና በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ አስመልክቶ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል።
የሕብረቱ ኮሚሽን ተጠባባቂ ጠቅላይ ጸሓፊ ኖሃው ቲያም በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ የሕብረቱ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይካሄዳል።
የሰላም፣ደህንነት እና አስተዳደር ጉዳዮች፣ ቀጠናዊ ትስስር እንዲሁም የህብረቱ የፈንድ ስርዓት በዋና አጀንዳነት ውይይት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የአፍሪካ ሕብረት የዘርፎች ዓመታዊ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ጠቅሰዋል።
በዚህም ሰብዓዊ ጉዳዮችና ፍልሰት፣ የወባ ወረርሽኝ እንዲሁም ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ ሪፖርቶች እንደሚቀርቡ ጠቅሰው ፥ ሪፖርቶችን ደግሞ በተወሰኑ የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የግብርና፣ ምግብና ስርዓት ምግብ ሪፖርት እንደሚያቀርቡም ጠቅሰዋል።
መሪ ሃሳቡ ስርዓተ ምግብ ላይ ቢያተኩርም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አይደረግም ማለት አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ በጉባኤው የአገር ውስጥ የጤና ዘርፍ ፋይናንስ፣ የአጀንዳ 2063 አፈጻጸምና የሕብረቱ የፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል፡፡
ጉባኤውን በተሳካ መልኩ ለማከናወን ከጉባኤው አስተናጋጅ አገር ኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከ19 60ዎቹ ጀምሮ የሕብረቱን ጉባኤ በተሳካ መልኩ የማስተናገድ ልምድ እንዳላትና የዘንድሮው ጉባኤም የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት የሕብረቱ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከጸጥታ ተቋማት ጋር የተቀናጀ ስራ መስራቱን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.