የአማራ ክልል በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ እንስሳት የመኖ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚሆን የእንስሳት መኖ ድጋፍ አድርጓል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ በሶማሌ ክልል የተከሰተውን የድርቅ ችግር በጋራ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ችግር በገጠመው ወቅት የሶማሌ ክልል ከጎኑ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ ለተደረገላቸው አቀባበል ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ለአንድነታችን በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ፤ የሶማሌ ወንድሞቻችን የድርቅ አደጋ የሁላችንም ቁስል በመሆኑ አይዟችሁ ልንላቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡
በጋራ መቆም በሚያስፈልገበት ወቅት በጋራ ቆመናል፤ በዚህም ድጋፍ የአንድነት ተምሳሌትነታችንን አሳይተናል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ።
የሶማሌ ክልል ድርቅ በተከሰተበት አካባቢ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እያደረገዉ ያለው ጥረት ያስመሰግናልም ብለዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው÷ አማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ቢደርስበትም ክልሉ ድጋፍ ማድረጉ አንድነታችንን እና መተሳሰባችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ካሁን ቀደም በነበረው ሥርዓት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ቢሠራም አሁን ሀገራዊ አንድነትን የሚያሳይ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡
አብሮ የመኖርና የመተባበር እሴት እየቀጠለ እንደሚገኝ የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ በጦርነቱም በጋራ በመቆም ድል መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ የአማራ ክልል ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡