ጨረራ አመንጪ ቁሶችንና መሳሪያዎችን የሚጠቀሙ ድርጅቶችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጨረራ አመንጪ ቁሶችንና መሳሪያዎችን የሚጠቀሙ ድርጅቶችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የጨረራ መከላከያ ባለስልጣን አመራሮች በባለስልጣኑ የስራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ውይይት ማካሄዳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱም የጨረራ መከላከል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው፥ የጨረራ እና የኒኩሌየር ቴክኖሎጂን ደህንነት በማረጋገጥ፣ ለሰላማዊ አገልግሎት እንዲውልና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፍበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም በላይ በበኩላቸው፥ ጨረራ አመንጪ ቁሶችንና መሳሪያዎችን የሚጠቀሙ ድርጅቶችን ግንዛቤ በማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ቁሳቁሶች ከጨረራ ጋር ያለውን ጥቅምና ጉዳታቸውን እንዲለዩና እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
አገልግሎታቸውን የጨረሱ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።