ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትሆንበት ወቅት ጀርመን ከጎናችን የምትቆም አገር ናት- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትሆንበት ወቅት ጀርመን ከጎናችን የምትቆም ሀገር ናት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡
በአምባሳደር ብርቱካን የተመራ ልዑክ በሁለተኛ ቀን የጀርመን ቆይታው ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት እና ደህንነት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በጀርመን በሚገነባው አዲስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሕንፃ በሚመለከት ውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያና ጀርመን የረጅም ዓመት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ ጀርመን ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ በምትሆንበት ወቅት ከጎናችን የምትቆም አጋራችን ናት ብለዋል፡፡
በጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነትና ያላቸውን ወዳጅነት የሚመጥን መሆን እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በጀርመን የኢትዮጵያ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያና በጀርመን መካከል እያደገ ስለመጣው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በንግድና በኢንቨስትመንት እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከሰጠው ትኩረት በመነሳት በርካታ ስራዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡
በጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት እና ሴኩሪቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመምጣቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሃላፊው ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና መሆኗንና ለአፍሪካ አንድነት የምታደርገው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡