ለሸኔ የሎጂስቲክ ስራ ሲያከናውኑ የነበሩ 8 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አስተዳደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለሸኔ የሎጂስቲክስ ስራ ሲያከናውኑ ነበሩ የተባሉ ናኒ ቤኛ የተባለ ግለሰብ እና ሰባት ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ግለሰቡ በክፍለ ከተማው ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጎሮ ሰፈራ የግለሰብ ቤት ተከራይቶ ለኦነግ ሸኔ የሎጂስቲክ ስራ ሲያከናውን እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል፡፡
ከግለሰቡ በተጨማሪ ሌሎች ሰባት ተጠርጣሪዎችም የተያዙ ሲሆን÷ ለሽብር አላማ ሊውሉ የነበሩ የቀድሞ መከላከያ የደንብ ልብስ፣ በርካታ ቁጥር ያለው የተለያዩ የባንክ ሂሳብ ደብተሮች፣ የተለያዩ የባንክ ኤቲኤም ካርድ እና የተለያዩ ሰነዶች በተከራዩበት ቤት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ በመከላከያ መረጃና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በተሰራ ስራ ነው የተያዙት፡፡
አከራዮች ቤታቸውን ሲያከራዩ የተከራዮችን ማንነት የሚገልጽ መረጃ ጠይቀው ማከራየት እንደሚገባቸው የጸጥታ ግብረ ሃይሉ አሳስቧል፡፡
ህብረተሰቡ ጸጉረ ልውጦችን ሲያገኝ በአቅራቢያው ላሉ የጸጥታ ሃይሎች ማሳወቅ ይጠበቅበታልም ተብሏል፡፡