በሐረሪ ክልል ለከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከ234 ሚሊየን ብር በላይ የበጀት ክለሳ እቅድ ፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ለከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም 234 ሚሊየን 693 ሺህ 902 ብር የበጀት ክለሳ እቅድ አፀደቀ።
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የዘጠኝ ወራት ስራ አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡
የበጀት ክለሳው ያስፈለገው ተጨማሪ በጀት የጠየቁት ፕሮጀክቶች በመኖራቸው መሆኑ ተገልጿል።
በወቅቱም የክልሉ የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈቲ ረመዳን የተቋሙን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
ስራ አስኪያጁ በሪፖርቱ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ከታቀደው 41ፕሮጀክቶች ውስጥ 26ቱ ስራቸውየተጠናቀቀ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ 15 ፕሮጀክቶች ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው።
በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የከተማ ተቋማት መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው በመሆኑን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አበረታች አፈፃፀም ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በማመላከት ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ፕሮጀክት ለማከናወን በጀት ወስደው የተሰወሩ ማህበራትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ሊሰራ እንደሚገባና አላስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን በማስቀረት የተስተዋሉ ጉድለቶችም ሊስተካከሉ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡