“ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት ይስጠን” አሉ የራያ እና አላማጣ ተፈናቃዮች
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ከራያ እና አላማጣ የተፈናቀሉ ዜጎች ተናገሩ።
በህወሃት የሽብር ቡድን ወረራ እና ግፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ከ28 ሺህ በላይ ዜጎች በሰሜን ወሎ ዞን ከድሬ ሮቃ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።
ከራያ ቆቦ፣ ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣ፣ ከአለማጣ ከተማ አስተዳደር ፣ ከራያ ኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ለበርካታ ወራት በችግር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከመንግስት እና ከለጋሽ ድርጅቶች የተወሰነ ድጋፍ የሚደረግ ቢሆንም ከአካባቢው የአየር ንብረት እና አቀማመጥ አንፃር ሲታይ የዕለት ምግባቸውን ለማሟላት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
በወር 15 ኪሎ ግራም ስንዴ እና ሩብ ሊትር ዘይት በመንግስት ይቀርባል ቢባልም፥ ይህም ወሩን ጠብቆ እየደረሳቸው እንዳልሆነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
በመንግስት ብቻ ሁሉን ነገር ለማሟላት አስቸጋሪ ነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ድርጅቶች ትኩረት ሊሰጡን ይገባል ነው ያሉት።
ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ እና ህዝቡ ከችግር እንዲወጣ እንደፍላጎታቸው ወደቀያቸው መመለስ ዋናው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህ ረገድም መንግስት አስፈላጊውን ጥረት ያድርግልን ሲሉ ጠይቀዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን በተፈጠረው ችግር ከ500 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ነበሩ ያሉት የሰሜን ወሎ ዞን የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ባለሙያ አቶ አወል ሐሰን አብዛኛውን ተፈናቃይ ወደቀየው መመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 51 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ 30 ሺህ የሚሆኑት ብቻ በመጠለያ ካምፕ ይገኛሉ ብለዋል።
መንግስት በመጠለያ ለሚገኙት ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፥የሚሰጠው የድጋፍ መጠን ግን የተፈናቃዮችን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም ብለዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ባለፍት 6 ወራት ሦስት ጊዜ መደበኛ ድጋፍ ለማድረግ የተሰራ ሲሆን፥ የስንዴ አቅርቦት የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ያማከለ ባለመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድ ለ4ኛ ዙር ለመስጠት ታስቧል ነው ያሉት።
በምንይችል አዘዘው