Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ድርቅን ለመቋቋም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተቀናጅታ እየሠራች ነው- አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ድርቅን ለመቋቋም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሠራች መሆኗን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

አቶ አደም ፋራህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሚስ ሃና ቴተህ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክራዋል፡፡

በዚህም በአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ያጋጠመውን ድርቅ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ እየተገበረች ያለውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የማስፋፋት ዕቅድ አውጥታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሠራች መሆኑን ነው አቶ አደም ፋራህ የተናገሩት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለዚህ የኢትዮጵያ ዕቅድ ድጋፍ እንዲያደርግም ልዩ መልዕክተኛዋን ጠይቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው÷ በመንግስት በኩል እስካሁን የተደረጉ ጥረቶችን እና የሰላም አማራጩ እውን እንዲሆን የተወሰዱ እርምጃዎችን አቶ አደም ገልጸዋል፡፡

መንግስት የህወሓትን ዓላማ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የነበሩ እስረኞችን መፍታቱ፣ ለሰብዓዊነት ሲባል የጊዜ ገደብ የሌለው የግጭት ማቆም ተግባራዊ መደረጉ፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ለሚመራው የሰላም ሂደት መንግስት ሙሉ ድጋፍ ማድረጉ ለሰላም አማራጩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን በአብነት ማብራራታቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ተወያይተው ሕገ መንግስታዊነትንና ሀገራዊ ጥቅምን ባስከበረ እና በአፍሪካ ሕብረት የተመራ የሰላም አማራጭ መከተል እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱም ርብርብ እንዲደረግ መወሳናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሌላኛዉ ወገንም የሰላም አማራጭን እንዲጠቀም የተባበሩት መንግስታት ግፊት ማድረግ እንደሚገባው አቶ አደም አመላክተዋል፡፡

ሚስ ሃና ቴተህ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በመቀናጀት ድርቁን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት አድንቀው የተባበሩት መንግስታት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ተልዕኮ ሰላም መገንባት በመሆኑ ተጨባጭ መረጃዎችን ለድርጅቱ በማቅረብ የሰላም ጥረቱን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.