በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወቅታዊ ፈተናዎችን በመቋቋም አበረታች የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል- አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወቅታዊ ፈተናዎችን በመቋቋም በተለያዩ ዘርፎች አበረታች የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።
የአፋር ክልል 6ኛ የክልል ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛመደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የ2014 በጀት ዓመትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በሪፖርቱ እንደተገለጸው÷ በበጀት ዓመቱ የሽብር ቡድኑ በሀገርና በክልሉ ላይ የደቀነውን ተጨባጭ የህልውና አደጋ ህብረተሰቡን አስተባብሮ በመምራት በአግባቡ መቀልበስ ተችሏል።
ከሽብር ቡድኑ አኳያ በጦርሜዳ ከተመዘገበው ድል በተጨማሪ÷ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዓለምአቀፍ መሀናኛ ብዙሃንና የዩኤን ኤጄንሲ ከፍተኛ አመራሮችን በመጋበዝ በጦርነቱ ዙሪያ እውነታውን በማስተዋወቅ ረገድ ስኬታማ ነበር ብለዋል።
ስለ ሽብር ቡድኑ ዓለም የነበረውን ብዥታና ተያያዥ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማረም በዲፕሎማሲው መስክም ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸው ተመላክቷል፡፡
የሽብር ቡድኑን ወረራ ከመመከት በተጎዳኝ መደበኛ የልማት ሥራዎችን በተለያዩ መስኮች በማከናወን አበረታች ውጤቶች መገኘቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ በእንስሳት ጤና አገልግሎት ዘርፍ ከ8 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ የቤት እንስሳት የበሽታዎች መከላከያ ክትባት ተሰጥቷል ብለዋል።
በተጨማሪም በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ከ93 ሺህ በላይ ሔክታር በተለያዩ አዝዕርቶች በመሸፈን ከ2 ነጥብ 1ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በማህበራዊ መሰረተ ልማት ዘርፍም÷ ከመደበኛ የልማት ሥራዎች በተጓዳኝ በሽብር ቡድኑ ወረራ የወደሙ ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለማስገባት ሰፊ ርብርብ መደረጉን አቶ አወል አብራርተዋል።
በንጹህ መጠጥ ውሃ ሴክተር ከተከናወኑ መደበኛ የልማት ሥራዎች በተጓዳኝ በወረራው ጉዳት ከደረሰባቸው 77 የውሃ ተቋማት ውስጥ 54 የውሃ ተቋማትን ከተለያዩ አጋር አካሎች ጋር በመተባበር ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል ብለዋል።
በተመሳሳይ በትምህርት ሴክተሩም በጦርነቱ ምክንያት ትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ ከ95 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ስኬታማ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም÷ የመደበኛ የጤና አገልግሎቱን ከማሻሻል በተጨማሪ በየመጠለያ ጣቢያው ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መደበኛ የጤና አገልግሎትን ከማዳረስ በተጨማሪ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል በህብረተሰቡ ጤና ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በወራሪው ኃይል ከወደሙ ሦስት ሆስፒታሎች፣ 44 ጤና ጣቢያዎች፣ 123 ጤና ኬላዎች መካከል 2 ሆስፒታልና 23 ጤና ጣቢያዎች ወደ አገልግሎት መመለስ መቻሉን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ አቅም ለማጎልበት በተሠሩ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ሪፖርቱ አመላክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።