የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችን የደቡብ ክልል መንግስት አደነቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችን የደቡብ ክልል መንግሥት “በሳል ውሳኔ” ሲል አድናቆት እና ምስጋና አቅርቧል፡፡
የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ከምባታ፣ ሀላባ እና ሀዲያ ዞኖች እንዲሁም የም፣ ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ ኧሌ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ክልል ሆኖ ለመደራጀት በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ የደቡብ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ÷ የአደረጃጀት ጥያቄው የሕዝቡን የቆየ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተሳሰብ፣ ብሎም ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማይጎዳ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን የክልሉ መንግስት በአድናቆት ተመልክቶታል ብሏል።
ከዚህ ቀደም የክልሉ መንግስት የሕዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር ዝንባሌ በማክበር የአደረጃጀት ጥያቄዎች በሕዝቦች መካከል ያለውን ብዝሃነት በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሷል መግለጫው፡፡
አሁን በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች በሳል ውይይት በማካሄድ ክልሉ የሚታወቅበትን ኅብረ ብሔራዊነት ለማስቀጠል ብሎም ከተናጠል ይልቅ በጋራ በመሆን መልማት እንደሚቻል የጋራ አቋም መያዙ በአብነት የሚጠቀስ ነው ብሏል የክልሉ መንግሥት በመግለጫው።
የክልል አደረጃጀት ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብሏል።
በፈተና ውስጥ እያለፍን የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት ይኖርብናል ያለው መግለጫው÷ የሕዝባችንን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በማስመልከት በምክር ቤቶች ደረጃ ውይይት በማካሔድ የቀረበውን አማራጭ ፍላጎት አስመልክቶ የክልሉ መንግስት አድናቆትና ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-