Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአንጎላ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የአንጎላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴቴ አንቶኒዮ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ከአንጎላ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሠራ ገልጸው÷ በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ በተለያዩ መስኮች ላይ ተባብሮ መስራት እና አማራጮችን ማስፋት ይገባል ብለዋል፡፡
“ዓለም በአይገመቴ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈች ነው፤ እንደ አህጉር የከፋ ተፅዕኖ እንዳያሳድርብን በጋራ ተባብረን መስራት ይገባል” ማለታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ ደመቀ ÷ መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የወሰዳቸውን የመተማመኛ እርምጃዎች ለሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን÷ ለአብነትም የተኩስ አቁም ስምምነት፣ያልተገደብ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ድርድር ቁርጠኛ በመሆን ተደራዳሪ ቡድን ሰይሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው÷ በማንኛውም ጊዜ የሰላም ድርድሩን ለመጀመር ዝግጁ ነው ብለዋል።

ከህወሓት ቡድን በኩል ግን የአፍሪካ ሕብረትን ጥረት የማጣጣል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የህዳሴው ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርን በተመለከተም÷ ኢትዮጵያ ድርድሩ በመርህ ላይ ተመስርቶ እንዲጠናቀቅ ያላትን ፅኑ አቋም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የአንጎላው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴቴ አንቶኒዮ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ ያጋጠማትን ችግር ለማለፍ እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች አድንቀዋል፡፡

“ኢትዮጵያ በነፃነት ትግላችን ወቅት ባለውለታችን ነች” ያሉት ሚኒስትሩ÷ ያን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚ ግንኙነት መለወጥ ይገባናል ነው ያሉት፡፡

በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለሚፈፀሙ የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ተፈጻሚነትም በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.