በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ የሚንቀሳቀስ ፎረም በይፋ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች በበላይነት የሚመሩትና በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ የሚንቀሳቀስ ፎረም በይፋ ሥራ ጀመረ።
የአንተርፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ደርጅት በይፋ ሥራ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመርኃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የፌደራልና የክልል መንግሥታት አመራሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች ተወካዮች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
ፎረሙ በንግዱ ማህበረሰብ አነሳሽነት መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም መቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን÷ ባለፉት ወራትም ህጋዊ ሰውነት የማግኘትና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ ዛሬ በይፋ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ፎረሙን በበላይነት የሚመሩ ሲሆን ÷የሀገሪቱ ታዋቂ ባለሃብቶች በመስራችነትና በአባልነት ተሳትፈውበታል።
ፎረሙ በኢትዮጵያና በኢጋድ ሀገራት በስፋት የሚስተዋሉ የሰላም እጦትና የደህንነት ስጋቶች እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን የንግዱ ማህበረሰብ በግንባር ቀደምትነት እንዲሰለፍ ለማድረግ መቋቋሙም ተጠቁሟል።
ፎረሙ የንግዱ ማህበረሰብ በሰላም ጠበቃነት ዙሪያ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና በተናጠልና በጋራ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረውና በቀጣናው የልማት ጉዳዮች የንግዱን ማህበረሰብ ትስስርና ተደማጭነት ለማጎልበት እንደሚሰራ መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!