በወ/ሮ ሙፈሪሃት የተመራ ልዑክ በእስራኤል የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢኖቬሽን ልምድ ልውውጥ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ የልዑካን ቡድን ከእስራኤል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራር ጋር ምክክር አደረገ።
ቡድኑ በእስራኤል በሥራ ዕድል ፈጠራና በኢኖቬሽን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ትናንትና እስራኤል የገባ ሲሆን ፥ ከእስራኤል መንግሥት አካላት ጋር መክሯል፡፡
ሚኒስትሯ ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ኢዳን ሮል ጋር የመከሩ ሲሆን፥ የሀገራቱ ወዳጅነት አሁንም በሁሉም መስክ ተጠናክሮ አንዲቀጥል የእስራኤል ድጋፍ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ምክትል ሚኒስትር ኢዳን በበኩላቸው ፥ ትብብሩን ይበልጥ ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ያለውን ፍላጎት ገልፀው፤ የእውቀትና ልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳአለው ብለዋል።
ትብብሩ ለሁለቱም ሀገራት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንና የኢትዮጵያን የወጣት አቅም በእሥራኤል ገበያ በማሰማራት መጠቀም አንደሚገባም ነው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የተናገሩት፡፡
በእስራኤል የመንግስት ፣ የአካዳሚክ እና የግል ዘርፍ የኢኖቬሽን ፖሊሲ ልምድ ያላቸው ኃላፊዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ፥ የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳርን ለማዳበርና ፈጠራን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመዋቅር፣ የፖሊሲ፣ የሕግ እና አስተዳደር ማዕቀፍን በሚመለከት ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የልዑካን ቡድኑ የእስራኤል የዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኃላፊዎችም ጋር ውይይት አድርጓል።
10 ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ይዞ የተንቀሳቀሰው የልዑካን ቡድኑ ፥ ከእስራኤል ሥራ ፈጣሪዎች ልምድ እንዲቀስሙና የገበያ ትስስርም እንዲፈጥሩ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
ልዑካን ቡድኑ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁንና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ባይሳ እና ባለሙያዎችን አካቷል።
የልዑካን ቡድኑ ምክክር ያተኮረው እስራኤል የቴክኖሎጂ፣ የግብርና፣ የጤና፣ የውሃ ሃብት አስተዳደር፣ የኢነርጂ ልማት፣ የትምህርት፣ የምርምርና የሙያ ሥልጠና ልምዷን ማካፈል በምትችልባቸው ዘርፎች ላይ ሲሆን ፥ የትብብር ሥርዓት ለመዘርጋት መግባባት ላይ መደረሱንም በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!