152 ስደተኞች ከጅቡቲ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) ጋር በመተባበር 152 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው መመለሱን አስታወቀ፡፡
ከተመላሽ ስደተኞቹ መካከል 19 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ፥ 50 የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዲሁም 14ቱ ሕፃናት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ሌሎች 14 ዜጎች ደግሞ ከጉዞ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የነበሩ እንዲሁም የህክምና ርዳታ ሲደረግላቸው የቆዩ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከተመላሽ ስደተኞች መካከል የተወሰኑት ከየመን ወደ ጅቡቲ የገቡ ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመሄድ አስበው ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እዛው ጅቡቲ የቀሩ ዜጎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ጅቡቲን እንደመሸጋገሪያ በማድረግ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት የሚፈልሱ ዜጎች በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የተለያዩ ብዝበዛዎችና በደሎች እንደሚደርሱባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡