ቴድሮስ አድኀኖም ለህወሓት ድምጽ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል – ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድኀኖም የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አፈ-ቀላጤ ሆኖ የመረጃ ጦርነቱን ሲመራ መቆየቱን ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን ገለጸ፡፡
አልስተር ቶምሰን ስኩፕ ሚዲያን ከመሰረቱት ጋዜጠኞች አንዱ ሲሆን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ነበረው፡፡
ጋዜጠኛ አልስተር ቶምሰን አሸባሪው ህወሓት በፈረንጆቹ ነሐሤ 25 ቀን 2020 ጦርነት ከከፈተ አንስቶ ቴድሮስ አድሃኖም ጋዜጠኞችን እየጠራ በቀጥታ በትግራይ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱን አንስቷል፡፡
በአንድ አጋጣሚ ዋሺንግተን ላይ ከአንድ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም ካለው ሪፖርተር ህወሓትን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፥ ትግራይ ለቤተሰቦቹ ገንዘብ መላክ ፈልጎ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ መናገሩን ጋዜጠኛው አስታውሷል፡፡
በወቅቱ ቴድሮስ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሹ አግባብ እንዳልነበረም ገልጿል፡፡
ምክንያቱም ይላል አልስተር ቶምሰን ÷ “ቴድሮስ አድኀኖም የተባበሩት መንግስታት “ነጻ” እና “ገለልተኛ” እንዲሆን የሚጠይቀውን የሰብዓዊ መርኅ ጥሷል” ብሏል፡፡
ሲጣሱ ሌሎች ላይ በተመድ እርምጃ የሚያስወስዱት መርሆዎች ቴድሮስ ላይ ግን ሲተገበሩ አልታየም ነው ያለው ጋዜጠኛው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች በጤናው ዘርፍ የደረሰውን ውድመት እና የአገልግሎት አቅርቦት ክፍተቶች መዝግቦ ሪፖርት ለማዘጋጀት የሚያደርገውን ጥረት ዋና ዳይሬክተሩ ለማበላሸት ብዙ ስለመሥራቱም መረጃዎች መኖራቸውን አስረድቷል፡፡
በአሸባሪው ህወሓት የተቀሰቀሰው ጦርነት ሕጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ቡድን እንዲረሸኑ እና እንዲደፈሩ ምክንያት መሆኑንም ገልጿል፡፡
በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ተመድ ቃል አልተነፈሰምም ያለው አልስተር፥ ለተፈጠረው አሰቃቂ ወንጀል ሁሉ ቴድሮስ አድኀኖም ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባውም አውስቷል።
ቴድሮስ አድኀኖም ሁልጊዜም የህወሓት አባል ሆኖ መቆየቱ አሁንም እንደሆነ ይታወቃል ሲልም አስምሮበታል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ እና ዓለማየሁ ገረመው