ዓለም ላይ 54 ሀገራት አስቸኳይ የብድር እፎይታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 54 ታዳጊ ሀገራትን ጨምሮ 25 ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ወደ አስከፊ ድህነት እንዳይገቡ አፋጣኝ የብድር እፎይታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስታወቀ።
ትናንት ድርጅቱ ባወጣው መረጃ ለኢኮኖሚ ቀውሱ ሀገራት እየሰጡት ያለውን ምላሽ በመጥቀስ፥ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ አመላክቷል፡፡
የብድር ዕዳ ጫናን ለማቃለል የሚረዱና ለብድር ማስተካከያዎችን ለማድረግ የሚያግዙ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመረጃው አካቷል።
እነዚህ 54 ሀገራት 18 በመቶ የሚጠጋውን የዓለም ህዝብ የሚገኝባቸው መሆናቸውን ያነሳው ፕሮግራሙ፥ ከዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብሏል፡፡
እንደ ፕሮግራሙ የሚያስፈልገውን የብድር እፎይታ አለማቅረብ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል።
የበለፀጉ ሀገራት የእዳ ጫናን ማስቆም የሚያስችል የሀብት ባለቤት መሆናቸውንም ነው ያነሳው።
የብድር እፎይታ ለታዳጊ እና ለበለጸጉ ሀገራት በእኩል ተግባራዊ ማድረግ የሚታሰብ አይደለም ማለቱን ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው አመላክቷል፡፡