የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያሳድጉ አስታውቀዋል፡፡
አባል ሀገራቱ ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡት፡፡
የዩክሬን አጋር የሆኑ 50 ሀገራት በኔቶ ዋና ጽህፈት ቤት ብራሰልስ ተገናኝተው በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት እና በተለያዩ ጉዳች ላይ መክረዋል፡፡
ዩክሬን ታሪካዊ ባለችው ከዚህ ውይይት በኋላም የኔቶ አባል ሀገራት ዘመኑን የዋጁ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎችን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በዚህ መሰረት አሜሪካ ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ ከፀረ ሚሳኤል በተጨማሪ የራዳር እና ሚሳኤል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም በቴክኖሎጂ የታገዘ አንድ የጀርመን ፀረ ሚሳኤል ዩክሬን መድረሱን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡
ብሪታኒያ ከሚሳኤል መቃወሚያው በተጨማሪ ለመረጃ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎቶች የሚውሉ በመቶዎች ሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንዲሁም ሌሎች ጦር መሳሪዎችን እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡
ካናዳ በበኩሏ 34 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ሳተላይትና ሌሎች ዘመናዊ ጦር መሣሪያዎችን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷ በዘገባው ተመላክቷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ አባል ሀገራቱ የፕሬዚዳንት ፑቲንን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ዩክሬን ራሷን ትከላከልበታለች የሚሉትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ይህ የኔቶ አባል ሀገራት ድርጊትም የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት አድማሱን እንዲያሰፋ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋትን አጭሯል።